8 minute read
ጌጡ ተመስገን ( የጉዞ ማስታወሻ )
የዓባይ ልጆች
ምንጭ - (በቅርቡ ለህትመት ከሚበቃ የተወዳጁ ጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን የጉዞ ማስታወሻ መጽሐፍ የተወሰደ)
Advertisement
ጐጃም፤ ደብረ ማርቆስ …
ከውሰታ በላይ፣ እነአገሬ ቤት ነን … አንጀት የሚያርሰውን የጐጃም ጠላ በ‹‹ሎጋው›› ብርጭቆ ሸጋ እንሸመጥጣለን …
የማይጠገበውን የ‹‹አቦይ›› ጨዋታ ከጣፋጭ ግብጦ ጋር እያዋሃድን አቦይ የሚያወጉንን የአባባ ይግዛው እውነተኛ ገጠመኝ በተመስጦ እናዳምጣለን፡፡
በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ - መንግስት …የቢቸናው አባባ ይግዛውና ባለቤታቸው አይናቸውን በአይናቸው አዩ።
‹‹ንጉሡ›› አሉት ልጃቸውን። ሁለተኛው ልጅ ተከተለ - ‹‹ኃይለ ሥላሴ›› ሲሉ ሥም አወጡለት። ሦስተኛው ልጅ መጣ - ‹‹ፀሐዩ›› ብለው ሰየሙት። አራተኛዋ ከተፍ አለች - ‹‹ጥሩ መንግሥት›› ብለው ጠሯት።
ንጉሡ ይግዛው ኃይለ ሥላሴ ይግዛው ፀሐዩ ይግዛው ጥሩ መንግሥት ይግዛው
ወታደራዊ መንግስት ንጉሡን ከዙፋናቸው አውርዶ በቮልስ ዋገን ሸኘና መንበረ ሥልጣኑን ተረከበ። ያሰጉኛል ባላቸው ላይ ሁሉ ሰበብ አስባብ እየፈለገ ‹‹አብዮታዊ እርምጃ›› መውሰዱን ተያያዘው፡፡ ወደ ብዙዎች የሚሰነዘረው የደርግ አብዮታዊ በትር፣ የሆነ ጊዜ ላይ ወደ አባባ ይግዛው ጐራ ብለው ስጋታቸውን ገለጹላቸው።
‹‹እኔ እምልህ ይግዛው … የነዚህን ልጆች ስም ብትቀይረው አይሻልም?›› አሉ ሰውዬው። ‹‹ለምን?!›› ሲሉ ጠየቁ አባባ ይግዛው፡፡
‹‹ይሄ ደርጉ … ‹ንጉሡ ይግዛው›፣ ‹ኃይለ ሥላሴ ይግዛው፣ ‹ፀሐዩ ይግዛው› እና ‹ጥሩ መንግሥት ይግዛው› … ሲባል የንጉሡ ወዳጅ ወይም ቤተሰብ መስለኸው እንዳይተናኮልህ ነዋ!›› በማለት መለሱ ሰውዬው፡፡
አባባ ይግዛው ጥቂት አሰብ አደረጉና እንዲህ አሉ …
‹‹እሱስ ልክ ነህ! … ግና የሁሉንም ልጆቼን ስም በመቀየር ከምደክም፣ የአንድ የራሴን ስም ብቀይር አይሻልም ትላለህ?›› …
‹‹ማን ብለህ ትቀይረው?›› ‹‹ቀለጠ!››
ንጉሡ ቀለጠ ኃይለሥላሴ ቀለጠ ፀሐዩ ቀለጠ ጥሩ መንግሥት ቀለጠ
ከአቦይ አንደበት የሰማነው ‹‹ስም ተኮር›› ወግ፣ የቢቸናው አባባ ይግዛው ግለሰባዊ ገጠመኝ ብቻ አይደለም። በመላው ጐጃም ለዘመናት የዘለቀ ትርጉም የሚሰጥ የስም አወጣጥ ልማድና ባህል አለ። ጐጃም ስም ሲያወጣ አስቦበት ነው። የጐጃም አባት በልጆቹ ስም ውስጥ ደስታውን፣ ሃዘኑን፣ ተስፋውን፣ ምኞቱን፣ ትዝብቱን፣ ቁጭቱን፣ ምሬቱን እና ብዙ አይነት ስሜቱን ያንጸባርቃል። የልጅ ስም ከአባቱ ብሎም ከአያቱ ስም ጋር፣ በወጉ ገጥሞና ትርጉም ይሰጥ ዘንድ በጥንቃቄ ተመርጦ ነው የሚሰየመው - በጐጃም።
ማለፊያ ተገኘ እያደረ አዲስ ባላገር አደመ አንተነህ ተስፋዬ መድኃኒት አገኘሁ ዳርእስከዳር ሞላ ተስፋዬ አበበ ጊዜው ከበደ አገሬ ምናለ ዘመኑ ዳኛቸው መልካምሰው ታዬ …
እንዲህ እና እንዲያ ያሉ ትርጉም አዘል ስሞች በብዛት ወደሚገኙባት ጐጃም የዘለቅነው፣ ሰውዬውን ፍለጋ ነው። አባይን የተሻገርነው ስም ከሚጋራው ከታላቁ ወንዝ ጋር በጥብቅ የተሳሰረውን፣ በልጆቹ ስም በኩል የዘመናት ቁጭትና ፀፀቱን ተስፋና ምኞቱን የገለፀውን የአቶ አባይን ዳና አነፍንፈን ለማግኘት ነው። ከማርቆስ ደምበጫ፣ ከቡሬ ዳንግላ፣ ከአዴት ገረገራ፣ ከሞጣ ደብረወርቅ ጐጃም ዙሪያ ገባውን ስናስስ ሰነበትን።
በስተመጨረሻ …
ራሱን ሰውዬውን ባይሆንም፣ የሰውዬውን ወላጆች አድራሻ ለማግኜት ቻልን። የአቶ አባይ ወላጆች አባባ ምህረት አለሙን እና እማማ ቢተውሽ ጠሃይነህ ወደሚኖሩባት ፊታችንን ወደ ደጀን አዙረን፣ ወብላት ጊዮርጊስ ማልደን ገሰገስን።
ABYSSINIA BUSINESS NETWORK ABN
IT'S OUR DAM
Getu Temesgen Getu Temesgen Media & Communications Managing Editor
እማማ ቢተውሽ ጥቁር እንግዳን በአክብሮትና በፍቅር ተቀብሎ ማስተናገድን ተክነውበታል።
በ1943 ዓ.ም. የወለዱት ሁለተኛ ልጃቸው አቶ አባይ ለልጆቹ ስላወጣቸው ‹‹ትርጉም አዘል›› ስሞች ሰምተን፣ አድራሻውን ፍለጋ እንደመጣን ነገርናቸው።
‹‹አይ! ... እሱኮ አዲሳባ ተገባ ዘመንም የለው! …›› አሉን እማማ ቢተውሽ። ይሄን ያህል ርቀት መድከማችን ሳያሳዝናቸው አልቀረም። ‹‹እኔ እምልዎት እማማ … ለልጃችሁ ‹አባይ› የሚል ስም ያወጣችሁለት በምን ምክንያት ነበር?›› አልኳቸው።
ፈገግ እንዳሉ ጥቂት አሰብ አደረጉና እንዲህ አሉኝ፤ ‹‹ዓባይ የሚለው ቃል በጣም ትልቅና
እንደ አባት በክብር የሚታይ ነው፡ ፡ ዓባይ ሁሉንም ነገር ይሰጣል፡ ፡ በኢትዮጵያውያን ዘንድ በጣም የተከበረ ወንዝ ነው፡፡ እግዚአብሔር እንደ ዓባይ ወንዝ የማያልቅ ሀብት ስለሰጠን፣ እኛም የልጃችን ስም ዓባይ አልነው››
አቶ አባይ የሚገኙበትን የአዲስ አበባውን አድራሻ ሰጡንና፣ በአክብሮትና ፍቅር እስከደጃፍ ድረስ ሸኝተውን ተሰነባበትን። *** ወደ አዲስ አበባ ተመልሰን፣ ዘነበ ወርቅ ተብሎ በሚጠራው ሠፈር ውስጥ ወደሚገኘው የአቶ አባይ ምህረት እና የባለቤታቸው ወ/ሮ ጥሩ ብርሃን መኖሪያ ቤት አቀናን። ከ1971 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያገለገሉትን የአቶ አባይ ምህረት፣ የስድስት ልጆች አባት ሲሆኑ፣ የሁሉም ልጆቻቸው ስም አወጣጥ ከዓባይ ወንዝ ጋር በቀጥታ የተቆራኘ ነው፡፡ ‹‹የሰው ማንነቱ ከስሙ ይጀምራል›› ይላሉ - አቶ አባይ፡፡ ይህን አባባላቸውን ከልጆቻቸው ስም አወጣጥ ጋር እያቆራኙ፣ ሁሉንም በዝርዝር አወጉን፡፡ ተፈራ ዓባይ ‹‹የዓባይ ወንዝ ውሃችንንና አፈራችንን ይዞ እየሄደ በዝምታ እናልፈዋለን፤ እንፈራዋለን፡፡ የዓባይ ወንዝ ዛፉንም፣ ግንዱንም፣ አፈሩንም ጠርጎ ለዘመናት ሲወስድ ማን ይናገረዋል?… በክረምት ወንዙ ሲሞላ ሰው ሁሉ ለመሻገር ይፈራዋል፡ በዚህ ምክንያት የመጀመሪያ ልጄን ተፈራ ዓባይ አልኩት››
ዱሮ ዱሮ ነው አሉ … አንዲት እናት ልጇ የዓባይ ወንዝን ሊሻገር ሲሞክር፣ በአደገኛው አዞ ተበልቶ ይሞትባታል።
‹ግባተ መሬቱን አትድገሙ እናንተ፣ ታዞ ሄዷል እንጂ ልጄ መቼ ሞተ› አለች አሉ እናት ሙሾዋን ስታወርድ።
የወንድሟ ሀዘን ልቧን የበላት እህትም፣ በሰም ለበስ ቅኔ እንዲህ
ስትል የውስጧን ስሜት ገለፀች …
‹ላንድ ቀን ትዕዛዝ ሰው ይመረራል፤ የእኔ ወንድም ታዞ ዓባይ ላይ ይኖራል›
አባት በበኩላቸው …
‹ልጄን አትጥሉብኝ ቢያዛችሁ ኅዳር 3 ቀን 1969 ዓ.ም. ተሹሞ፣ አዞ አያውቅምና ከዚህ አስቀድሞ› የአቶ ዓባይ ምሕረት የበኩር በማለት ሙሾዋቸውን ሞሸሹ፡፡ ልጅ ተወለደ። ስሙም ተፈራ ዓባይ ይባላል፡፡ የስሙን አወጣጥ በተመለከተ አባትዬው ሲናገሩ እንዲህ ይላሉ፦ ‹‹አባቴ! ሕልሙን እየኖረ ነው›› ይላል የአቶ አባይ ምህረት የበኩር ልጅ ተፈራ ዓባይ ስለ አባቱ ሲናገር። *** 72 Abyssinia Business Nework // ABN ልዩ እትም 2012 Special Edition of GERD 2020
- ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ (1957ዓ.ም)
ስንታየሁ ዓባይ
ጥር 11 ቀን 1973 ዓ.ም.
የአቶ ዓባይ ምሕረት ሁለተኛ ልጅ ተወለደች - ‹‹ስንታየሁ›› ተባለች፡፡
‹‹የዓባይን ወንዝ ብዙ ሰዎች ከየአቅጣጫው እየመጡ ያዩታል፡ ፡ አገር ጎብኚዎች፣ ተመራማሪዎች የጎጃም ምድርን በረገጡ ቁጥር በወንዙ ይደመማሉ፤ ስለ ወንዙ ያወጋሉ፡፡ ከዚህ ተነስቼ ነው ሁለተኛዋን ልጄን ስንታየሁ ዓባይ ያልኳት›› ይላሉ አቶ አባይ።
ፍቼ፤ ገርበ ጉራቻ ከተማ፣ ኮማንደር ሠፈር ዘልቄ ያገኘኋት ስንታየሁ ስለ አባቷ እንዲህ ስትል ነገረችኝ፤ ‹‹አባቴ ሁልጊዜ በአባይ ወንዝ እንደተብሰከሰከ፤ እንደተቆጨ ነው፡፡ በዓባይ ወንዝ ዙሪያ ከሚሰማውና ከሚያየው ተነስቶ፣ ‹‹ስንታየሁ አባይ›› አለኝ፡ ፡ ስሜ ከአባይ ጋር የተቆራኘ በመሆኑ እኮራበታለሁ፡፡ ለአባቴም ታላቅ አክብሮትና ምስጋና አለኝ››
ABYSSINIA BUSINESS NETWORK ABN
ተናኘ ዓባይ
ሰኔ 20 ቀን 1975 ዓ.ም.
የአቶ ዓባይ ምህረት ሦስተኛ ልጅ ወደዚህች ዓለም መጣች። አባቷ ተናኘ ሲሉ ሥም አወጡላት - ተናኘ ዓባይ፡፡ ዓባይ እርሷ ከመምጣቷም በፊት ሆነ ከመጣች በኋላ እየፈሰሰ፣ ከድንጋይ ድንጋይ እየዘለለ፣ እየተላተመ፣ አንገቱን ደፍቶ፣ ድምፁን አጥፍቶ ከመጋለብ አልቦዘነም፡፡
‹‹የዓባይ ወንዝ አፈሩን፣ ውሃውን
ኢትዮጵያ
ይዞ ሱዳንና ግብጽ ለዘመናት ናኝቷል፤ ሄዷል፡፡ ተናኘ የሚለው ሥም፤ የዓባይ ወንዝ በኢትዮጵያ ላይ ያሳደረውን ቁጭት ይገልጻል›› ይላሉ የተናኘ እናት ወ/ሮ ጥሩ ብርሃኑ፣ የሦስተኛ ልጃቸውን የሥም አወጣት ሲገልፁ።
የግብፅ ሕይወት ዓባይ
ታህሳስ 13 ቀን 1977 ዓ.ም.
የአቶ ዓባይ ምሕረት አራተኛዋ ልጅ፤ የግብፅ ሕይወት ዓባይ ተወለደች፡ ፡ አዳማ በፒኮክ ጠጠር መንገድ ተጉዘን አገኘናት፡፡
‹‹አባታችን የሦስት ወንዶችና የሦስት ሴቶች ልጆቹን ስም ከዓባይ ወንዝ ጋር አያይዞ ነው ያወጣው፡፡ እኔ የግብጽሕይወት ዓባይ የሚለውን ስሜን በጣም እወደዋለሁ፡፡ የግብጽ ሕይወት ዓባይ፡፡ እውነት ነው፤ የግብጽ ሕይወት የዓባይ ወንዝ ነው፡ ፡ የኢትዮጵያ ሕይወት ግን የዓባይ ወንዝ አልሆነም›› አለችን፡፡ ግብፃውያን የሕይወታቸው መሠረት ለሆነው የዓባይ ወንዝ ከ10 ሺህ በላይ ዜማዎችን አቀንቅነውላታል፡፡ የእኛ ሀገሯ ባለቅኔ፤ እጅጋየሁ ሽባባው ደግሞ፣ዘመን ተሻጋሪ በሆነው ድንቅ እና ጥልቅ ዜማዋ ‹‹የማያረጅ ውበት የማያልቅ ቁንጅና›› ስትል ዓባይን ታሞካሽዋለች፡፡ ደግሞም መለስ ብላ ታሽሟጥጠዋለች፡፡
‹‹… ብነካህ ተነኩ አንቀጠቀጣቸው፣ መሆንህን ሳላውቅ ሥጋና ደማቸው፤ የሚበሉት ውሃ የሚጠጡት ውሃ፣ ዓባይ ለጋሲ ነው በዚያ በበረሃ፤ … አንተ ወራጅ ውሃ ቢጠሩህ አትሰማ፣ ምን አስቀምጦኃል ከግብጾች ከተማ?... ››
ይገደብ ዓባይ
መጋቢት 23 ቀን 1984 ዓ.ም.
ሰማይ በወገግታ ሲጣቀስ፣ የምድረ ኢትዮጵያ የተስፋ ጡቶች ሲያግቱ፣ የአቶ ዓባይ ልብ ትርታ ተጨምቆ ጠብ ያለው ምኞታቸው፤ ይገደብ ዓባይ የሚል ነበር፡ ፡ እንደለመዱት ህልምና ራዕያቸውን በአምስተኛው ልጃቸው ውልደት አወጁት፡ ፡ የአብራካቸውን ክፋይ ‹‹ይገደብ ዓባይ›› ብለው በመሰየም ትንቢት አዘል ቀጭን ትዕዛዝ አስተላለፉ፡ ፡ የዘመናት ምኞታቸውን በደማቅ ቀለም አኖሩ፡፡
የአቶ ዓባይ ባለቤት ወ/ሮ ጥሩ ብርሃኑ ከልጃቸው ሥም ጋር የተያያዘ ገጠመኛቸውን እንዲህ አወጉን፦ ‹‹ልጄን ይገደብን የራስ ሕመም ይዞት አለርት ሆስፒታል ወሰድኩት፡፡ ካርድ ለማውጣት በመስኮት ቆምኩ፡ ፡ ነርሷ ‹የታካሚው ስም?› ብላ ጠየቀችኝ፡፡ ‹ይገደብ ዓባይ› አልኳት፡፡ እየሳቀች ጻፈችው፡ ፡ ተራው ደርሶ ወደ ሕክምና ክፍሉ ለመግባት ነርሷ ስሙን ዳግም መጥራት ጀመረች፡ ፡ ‹‹ይገደብ ዓባይ፤ ይገደብ ዓባይ›› አለች፡፡ ‹ያንቺ ልጅ ነው?› ብላ ጠየቀችኝ፡፡ ‹አዎ› ስላት ‹አልሽውና› ብላ ታካሚውን ሁሉ አሳቀችው፡፡››
ተፈራ ዓባይ ‹‹አባታችን ሕልሙ እውን እየሆነ ነው›› ብሏል፡፡ የግብጽ ሕይወት ደግሞ ‹‹በፊት የስማችን አወጣጥ ብዙም አያስደንቀኝም ነበር፡፡ ሰው በስማችን ለምን እንደሚደነቅ ግራ ይገባኝ ነበር፡ ፡ በአባቴ የስም አወጣጥ፤ ከዓባይ ወንዝ ጋር የተቆራኘው የታሪክ ሰንሰለት አልገባኝም ነበር፡፡›› አለች እየተቆጨች፡፡
‹‹አባቴ የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ ከመቀመጡ ከ19 ዓመት በፊት ‹ይገደብ› የሚል ስም ለእኔ ማውጣቱ አስደንቆኛል። ከቤተሰቡ ክብር ይልቅ የሀገሩን ክብር እንደሚያስቀድም በልጆቹ ስም አወጣጥ አስመስክሯል፡ ፡ አባቴ ከ19 ዓመታት በፊት የኢትዮጵያን ህዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ በእኔ በልጁ ስም ላይ አስቀምጧል፡ ፡ በዚህ አጋጣሚ አባቴን በጣም አመሰግነዋለሁ፤ አከብረዋለሁ፤ አደንቀዋለሁ፡፡›› ይላል ይገደብ ዓባይ።
ይገደብ ዓባይን ‹‹ስምህ አሁን ወቅቱን ጠብቃ የተበጀች ናት! የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ ከመቀመጡ 19 ዓመታት በፊት አልወጣልህም›› የሚሉ ተከራካሪዎች በተደጋጋሚ ያጋጥሙታል፡፡ በዚህን ጊዜ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ሰርተፍኬት ወይም የሚኒስትሪ ካርዱን በማሳየት ስሙ ነባር እንጂ አዲስ የወጣለት አለመሆኑን ያስረዳል፡ ፡ ተከራካሪዎችም ይረቱና ‹‹ይገርማል! … ይደንቃል!›› በማለት ይጨብጡታል፤ ያቅፉታል፡፡
ABYSSINIA BUSINESS NETWORK ABN
የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ፕሮጀክት የመሠረት ድንጋይ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉባ ወረዳ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም. በክቡር አቶ መለስ ዜናዊ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግሥት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ተቀመጠ፡፡
ይታያል ዓባይ
ሐምሌ 22 ቀን 1987 ዓ.ም.
ያቆጠቆጠው ተስፋ መዓዛው እየቀረበ መጣ፤ የፍርሃቱ ጥቁር ሰማይ በብርሃን ውበት ሲገፈፍ ልባቸው የሞላው አቶ ዓባይ ምሕረት ህልማቸው እውን የሚሆንበት ቀን መድረሱን በልጃቸው ስም ገለጡት፡ ፡ ስድስተኛ ልጃቸውን፤ ይታያል ዓባይ ብለው ስም አወጡለት፡፡
የእነ ተፈራ አባይ እናት ወ/ሮ ጥሩ ብርሃኑ ‹‹ስድስተኛውን ልጅ ይሄነው ዓባይ ልንለው ፈልገን ነበር፡፡ ነገር ግን ይታያል ዓባይን አስቀደምን›› ሲሉ ስለ ሥም አወጣጡ ገልፀዋል፡፡ ይታያል ዓባይ በበኩሉ፤ …
‹‹ዓባይ ሥም ነው እንጂ ምን ጠቅሟል ላገሩ፣ ትርፉ ለሌላ ነው ሄዶ መገበሩ፡፡ ›› … የሚለው ሥነ ቃል ሊቀር ነው መሰል›› አለ - ከራሱ ሥም አወጣጥ ጋር በማያያዝ፡፡ ‹‹ይታያል ዓባይ›› የሚለው ሥም ትርጉሙ ‹‹እውን ይሆል፤ ይገደባል፤ ይታያል›› የሚል መልዕክት ያዘለ ነው፡፡
የዓባይ ልጆች ብዙ ናቸው …
ለልጆቻቸው ከዓባይ ጋር የተቆራኘ ሥም ያወጡት አቶ ዓባይ ምሕረት ብቻ አይደሉም፡፡ የወሎ ዞን ወረኢሉ ከተማ ገበያ ዳር ሠፈር አቶ ዓባይ ፍስሃም በልጃቸው ስም የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡ የአራት ልጆቻቸው ስም፦ ‹‹ራሔል ዓባይ፣ ይገደብ ዓባይ፣ ኅሩይ ዓባይና ቤተልሄም ዓባይ ነው፡፡ አዲስ አበባ ቡልጋሪያ ማዞሪያ የሚኖሩት ቤተሰቦች፤ ለልጆቻቸው ዘላለም ዓባይ፣ ቅድመዓለም ዓባይ፣ ረድኤት ዓባይ፣ የግብጽሕይወት ዓባይና ይገደብ ዓባይ የሚሉ ሥሞችን አውጥተውላቸዋል፡፡ እነዚህ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት በዓባይ ወንዝ ግራና ቀኝ ሲዋዥቁ፣ ከላይ ታች፤ ከታች ላይ መማሰናቸውን ማሳያ ነው፡፡
‹‹እስመ ስሙ ይመርሖ ሀብ ግብሩ›› ስሙ ወደ ግብሩ (ተግባሩ) ይመራዋል(ና)…
ቤተሰብ ማለት አገር ማለት ነው፡፡ አገር የቤተሰብ ድምር ውጤት ነው፡፡ * * * ‹‹ይታያል ዓባይ፡፡››፣ ‹‹ይታያል ዓባይ!››፣ ‹‹ይታያል ዓባይ?››