5 minute read
ፍራንሲስ ፋልሴቶ
ፈረንሳዊው ፍራንሲስ ፋልሴቶ በ1970ዎቹ አጋማሽ አካባቢ ከጥቂት ጓደኞቹ ጋር በመሆን በፈረንሳይ ዋና ከተማ ፖሪስ የሙዚቃ ኮንሰርት ማዘጋጀት ጀመረ፡፡ ይህን ያከናውኑ የነበሩት በአንድ ለትርፍ ያልተቋቋመ መንግሥታዊ ድርጅት /NGO/ አማካኝነት ሲሆን የሚቀርቡት ሙዚቃዎች ደግሞ ከመላው ዓለም የተውጣጡ የፍሪ ጃዝ /free jazz/፣ የድምፅ ሙዚቃ / noise music/፣ ኢንዱስትሪያዊና ባህላዊ ሙዚቃዎች ነበሩ፡፡
ዘመናዊ የኢትዮጵያ ሙዚቃ የተሟላ ስዕል ሊሰጥ ይችላል የተባለውና በቡዳ ምዩዚክ የተካተተው ተከታታይ የኢትዮጲክስ ሲዲ አዘጋጅና ፈጣሪ ነው፡፡ ፍራንሲስ ፋልሴቶ፡፡ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ የ1960ዎቹ ማገባደጃና የ1970ዎቹ መግቢያ በጣም ውጤታማና ምርታማ ዘመን ተብሎ የሚጠቀስ ነው፡፡ ኢትዮጲክስ ጥቂት ባህላዊ ሙዚቃዎችንና የደርግ መንግሥት ውድቀት ድረስ የተሰሩ ጥቂት ሙዚቃዎችን ያካተተ ነው፡፡ ፍራንሲስ ፋልሴቶ አቢሲኒ ስዊንግ ኤ ፒክቶሪያል ሂስትሪ ኦፍ ሞደርን ኢትዮጵያን ምዩዚክ /Abyssinie Swing: A Pictorial History of Modern Ethiopian Music/ የተሰኘ በሻማ ቡክስ የታተመ ቆንጆ መፅሐፍ ደራሲ ነው፡፡
Advertisement
“እ.ኤ.አ. በኤፕሪል ወር 1985 ዓ.ም በአንድ የቀን ሁለተኛ አጋማሽ /ከሰዓት በኋላ/ ነበር አዲስ አበባ ወደሚገኘው ታንጎ ሙዚቃ ቤት የሄድኩት፡፡ “መሐሙድ አህመድ ከአይቤክስ ባንድ ጋር” የሚል ርዕስ ካለው የKF 20 ሸክላ የጀርባ ሽፋን ያገኘሁት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የማውቀው ብቸኛ አድራሻ ነው ሙዚቃ ቤቱ፤ ዓሊ በሙዚቃ ቤቱ ውስጥ ነበር፡፡ ማን እንደሆንኩና ወደ ኢትዮጵያ ለምን እንደመጣሁ ወዲያው ነው ያወቀው፤ ድምፃዊ መሐመድ አህመድን ለማግኘትና ድምፃዊው በአውሮጳ የሙዚቃ ዝግጅት እንዲያቀርብ ለመነጋገር
መሆኑ ገብቶታል፡፡” በማለት የሚያስታውሰው ፍራንሲስ ፋልሴቶ በመቀጠል “በዕለቱ ዓሊ ወደ መኖሪያ ቤቱ ይዞኝ ሄደ፡፡ ምሽቱን በሙሉ ስናወራ ነጋ፤ ፀሐይ እስክትወጣ፤ ምንም እንቅልፍ አልነበረንም፤ በጣም ትልቅ አጋጣሚ፤ ስለ ኢትዮጵያ ሙዚቃ ዕድገትና መሻሻል ለመነጋገር በጣም ትልቅ አጋጣሚ ነበር” በማለት ይገልፃል፡፡
ፍራንሲስ ፋልሴቶ እ.ኤ.አ. በ1997 ዓ.ም የኢትዮጲክስ ተከታታይ ሙዚቃ የመጀመሪያ አልበም ባዘጋጀበት ወቅት
አብዛኛው የውጪ ዜጋ ስለ ኢትዮጵያ ሙዚቃ በቂ እውቀት አልነበረውም፡፡ ለሁለት ተከታታይ አስርት ዓመታት ፋልሴቶ ኢትዮጵያን በዓለም የሙዚቃ ካርታ ላይ የማስቀመጥ ኃላፊነት የተጣለበት ብቸኛ ባለሙያ ነበር፡፡
ፋልሴቶ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ፍቅር የወደቀው እ.ኤ.አ. በ1984 ዓ.ም የሙዚቃ ኮንሰርት አዘጋጅ /promoter/ በመሆን በፓይቲየርስ በሚሰራበት አጋጣሚ የመሐሙድ አህመድን “መላ መላ” የሚለውን ዜማ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰማበት ወቅት ነበር፡፡
ከዚያ በኋላ ፍራንሲስ ፋልሴቶ ወደ አዲስ አበባ ተከታታይ ጉዞ አደረገ፡፡ በኢትዮጵያ በ1960ዎቹና 70ዎቹ ወርቃማ ዘመን የተሰሩ የሙዚቃ ቅጂዎችን ማዳመጥና መመርመር ጀመረ፡፡
ዓሊ አብደላ ኬይፋ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ዕድገት ያደረገውን አስተዋፅዖ በተመለከተ ፋልሴቶ ሲናገር እ.ኤ.አ. በ1980ዎቹ አጋማሽ ዓሊ የኢትዮጵያ የሙዚቃ አታሚዎች ንጉስ፣ የሰላ የሙዚቃ ችሎታ ያለው፣ በሀገሪቱ የሙዚቃ ዘርፍ ዋና ተዋናይና በቴክኖሎጂና ፈጠራ ፍቅር የወደቀ በማለት ይገልፀዋል፡፡
ዓሊ ታንጎ እንደ ዓሊ ቢራ፣ ብዙነሽ
በቀለ፣ አለማየሁ እሸቴ፣ አያሌው መስፍን፣ ሙሉቀን መለሰ፣ መሐሙድ አህመድ፣ አስቴር አወቀ፣ ሐመልማል አባተ፣ ንዋይ ደበበና ህብስት ጥሩነህ የመሳሰሉ ዋና ዋና ኢትዮጵያዊ ድምፃውያንን ታላላቅ ሥራዎች በማሳተምና ለአድማጭ በማድረስ ትልቅ ሚና ስለተጫወተ ከፍተኛ ክብር ይገባዋል ብሏል ፋልሴቶ፡፡
በኋላ ዓሊ አብደላ ኬይፋ /ዓሊ ታንጎ/ በአሁኑ ወቅት ከመላው የሙያ አጋሮቹ፣ ጓደኞቹ፣ ቤተሰቦቹና ከሙዚቃ አድናቂዎች እውቅናና ክብር ሊሰጠው ይገባል፤ ዓሊ ለዘላለም ይኑር! በማለት ምኞቱን ገልጿል፡፡
“በኢትዮጵያ ማህበረሰብና ባህል ውስጥ ለበርካታ ዓመታት እንደቆየ አንድ የውጪ ዜጋ ዛሬ ላይ ሆኜ ስለ ዓሊ መናገር የምችለው ዓሊ ክፍት አዕምሮ ያለውና ከፍተኛ የሙያ ፍላጎት ያለው መሆኑን ነው፡፡” ካለ
ዳዊት ይፍሩ ከአራት አስርት ዓመታት በላይ በሙዚቃው ዓለም የቆየው፤ በዋናነት በዳህላክና በሮሃ ባንድ የሙዚቃ ባንዶች ሙዚቃ በመጫወት በህዝብ ዘንድ አንቱታን ያተረፈው ታዋቂው የሙዚቃ ሰው ዳዊት ይፍሩ ከአቶ ዓሊ ጋር የተዋወቁት ከዛሬ 42 ዓመት በፊት በ1070 ዓ.ም ውጤታማ የነበረውን የሙሉቀን መለሰ ‘ሀገሯ ዋሳ መገና’ የተሰኘው የሙዚቃ አልበም በሚዘጋጅበት ጊዜ ነበር፡፡ “በወቅቱ ይህ የሙሉቀን መለሰ ሙዚቃ በዳህላክ ባንድ ሲሰራ ቅንብሩን በሙሉ የሰራሁት እኔ ነኝ፡፡” ያለው ዳዊት ይፍሩ ሮሃ ባንድ ስራ ከጀመረ በኋላ ከዓሊ ኬይፋ ሪከርዲንግስ ጋር የሰራቸውስራዎች በርካታ ሲሆኑ የንዋይ ደበበ፣ ሀመልማል አባተና ህብስት ጥሩነህ የመሳሰሉ ድምጻውያን ስኬታማ ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ሙዚቀኞች ወደ ሙዚቃ ባንዶች እንዲሁም ድምጻውያን ወደ ባንዶች የሚመጡበት ስርዓት ራሱን የቻለ ሂደት
ነበረው፡፡ “ በዚያን ግዜ ዘፋኞችን መርጦ ወደ ሙዚቃ ባንዶች የሚያመጣው ዓሊ ታንጎን የመሳሰሉ ሙዚቃ አዘጋጅተው የሚያከፋፍሉ ሙዚቃ ቤት ያላቸውየሙዚቃ አዘጋጆች /producers/ ናቸው፡፡ ” ይላል ዳዊት ይፍሩ፡፡
ድምጻዊ ንዋይ ደበበ እራሱ ግጥምና ዜማ የሰራላቸውን ዘፈኖች ይዞ መጀመሪያ የሄደው ወደ ዓሊ ነበር፡፡ ዓሊም በቅድሚያ የንዋይ የመጀመሪያ የነበረውን ሙዚቃ አዳመጠ፣ ችሎታውን ተረዳ፣ ከዚያም ወደ ሮሀ ባንድ ይዞ መጣ፡፡ ንዋይ ከዚያ በፊት ምንም ዓይነት የዘመናዊ ሙዚቃ ስራ ልምድ የሌለውና ከራስ ቲያትር ባህላዊ የሙዚቃ ባንድ ጋር ይሰራ ስለነበር ከሮሀ ባንድ ጋር ሙዚቃዊ ውህደት ለመፍጠር ብዙ ጥረት ይጠይቅ ነበር፡፡ከብዙ ጥረትና ድካም በኋላ የንዋ አልበም ለህዝብ ይፋ ሆነ ፡፡ንዋይ ደበበም በዚህ የመጀመሪያ አልበሙ በሀገር ውስጥና በዓለማቀፍ ደረጃ በማይታመን መልኩ ዝነኛ ሆነ፡፡
Photo by Daniel Tiruneh
ዓሊ በወቅቱ በአንድ ዴክ የሚሰሩ ስራዎችን በተወሰነ ደረጃ ወደ ዘመናዊ ደረጃ ለማሳደግ የሚያስችሉ ዘመናዊ የሙዚቃ መቅጃ መሳሪያ እንደነበረው ዳዊት ያስታውሳል፡፡ዓሊ ዘፋኞችን እጅጉን ያበረታታ ነበር፤ በክፍያ ረገድም ቢሆን ወቅቱ ይጠይቅ የነበረውን ክፍያ ያለምንም ማንገራገር ይከፍል ነበር፡፡ በተለይ የአንድ ድምጻዊ አልበም ስኬታማ ከሆነና፤ በድጋሚ የታተመ ከሆነ ማበረታቻ ያደርጋል፤ ይሸልማል፤ለድምጻዊውም ተጨማሪ ክፍያ ይፈጽማል፡፡ “ ይህ ድርጊቱ ደግሞ ዓሊ ከድምጻውያን ጋር በቀጣይ አብሮ ለመስራት ምቹ ሁኔታን ከመፍጠሩ በተጨማሪ ቤተሰባዊ ቅርበት እንዲኖር አድርጓል፤ በዚህም የተነሳ ሮሀ ባንድ ከዓሊ ጋር በርካታ ስራዎችን ሰርቷል፡፡ ” ብሏል ዳዊት ይፍሩ ፡፡
ዓሊ እንደ ሙዚቃ አዘጋጅነቱ ትርፍ ሊያስገኝለት በሚችል ስራ ላይ ያተኩር ነበር፡፡ የሮሃ ባንድ ሙዚቃ ተጫዋቾች ደግሞ የሙዚቃው ውበትና ጥራት ላይ በመጨነቅ በትብብር ነበር የሙዚቃ ስራዎች ይሰሩ የነበሩት፡፡ “ ዓሊ በጣም
ይገርመኝ የነበረው ያዘጋጀውን የሙዚቃ ስራ ወይም አልበም በአዲስ አበባ ብቻ ተወስኖ እንዲቀር አይፈልግም ነበር፡፡ ከአዲስ አበባ ውጪ በነበረው ግንኙነት/ connection/አማካኝነት ካሴቶችን በየክፍለሀገሩ ያደርስ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ደግሞ የካሴት ተጠቃሚዎች የነበሩት በዋናነት በየበረሀውና በየገጠሩ የነበሩ ወታደሮችና መምህራን ነበሩ፡፡ ይህ የሙዚቃ ስራዎችን ለእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲደርስ የማድረግ ተግባር የሚመሰገንና የሚደነቅ ትልቅ ችሎታ ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡” ሲል ሙዚቀኛ ዳዊት ይናገራል፡፡
በወቅቱ በአዲስ አበባ የነበሩት የሙዚቃ ቤቶች ቁጥር ውስን ቢሆንም እርስ በእርስ በሚደረግ የገበያ ውድድር ድምጻውያንን የማስኮብለልና የመሻማት ሁኔታ ይስተዋል ነበር፡፡ በመሆኑም ለድምጻውያን ተገቢውን እንክብካቤ ማድረግ፣ የሚገባውን ክብርና ክፍያ መስጠት፤ ከዚያም የድምጻውያኑ ስራ በአግባቡ ወደ ህዝብ እንዲደርስ ማድረግ ወሳኝ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ዓሊ ኬይፋ ከፍተኛ ጥረት ያደርግ ነበር፡፡
በሮሀ ባንድ የተቀናበረው የሀመልማል አባተ የመጀመሪያ አልበም ከመውጣቱ በፊት የሙዚቃ ባንዱ በምሽት ክበብ
ውስጥ በሳምንት ሁለት ጊዜ ይጫወት ስለነበር ዓሊ ድምጻውያኗ ስራዋን ለህዝብ እንድታስተዋውቅ በመፈለጉ፤ ደምወዝ እራሱ እየከፈላት በዚያ ምሽት ክበብ እንድትጫወት አደረገ፡ ፡ ይህ ሁለት ጠቀሜታ አለው ይላል ሙዚቀኛ ዳዊት ይፍሩ፡፡ “ አንደኛ ሀመልማል ካሴቷ ከመውጣቱ በፊት ከህዝብ ጋር ያስተዋውቃታል፤ ሁለተኛ ደግሞ ከዚያ በኋላ የምታወጣው ካሴት ደግሞ የበለጠ ተፈላጊ ይሆናል ማለት ነው፤ይህ አሰራር ደግሞ የብልህ ነጋዴ ስትራቴጂ ነው፡፡”
ዓሊ ኬይፋ በተፈጥሮ የተቸረውን የንግድ ፈጠራ ክህሎት በመጠቀም ድምጻውያኑንም ሆነ እራሱን ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት ያደረገ ስኬታማ የሙዚቃ አዘጋጅ ነው፡፡ ንዋይ ደበበ የመጀመሪያ አልበሙን ካወጣ በኋላ ከሮሀ ባንድ ጋር በመሆን በፈረንሳይ የኣለማቀፍ ፌስቲቫል ላይ እንዲሳተፍ አድርጓል፡፡
ከሮሀ ባንድ ወይም ከድምጻውያን ጋር ከነበረው መልካም ግንኙነት በተጨማሪ ዓሊ አለመግባባት ውስጥ ገብቶ የነበረበት ጊዜ ስለመኖሩ ለቀረበለት ጥያቄ አርቲስት ዳዊት ይፍሩ ሲመልስ
“ ዓሊ እኔ እስከማውቀው ድረስ ከእርሱ ጋር የሰሩ በርካታ ድምጻውያንን ለካሴት ስራ ወደ ሮሀ ባንድ ይዞ ሲመጣ ምንም ዓይነት ያለመግባባትና ግጭት ተከስቶ አያውቅም ፡ ፡” ብሏል፡፡
አሁን ጊዜው እነ ዓሊ ያደርጉ እንደነበረው ግጥምና ዜማን አሰባስቦ፤ ድምጻውያንን ወደ ሙሉ ባንድ አምጥቶ ካሴት የሚሰራበት ዘመን አይደለም፤ ያም ጊዜ ተመልሶ ሊመጣ አይችልም፡፡ በመሆኑም እንደ ዓሊ ዓይነት አሳታሚዎች የፈጠራ ክህሎታቸውን በማሳደግ፤ ኢንተርኔት፣ ዩትዩብና የመሳሰሉ ቴክኖሎጂዎችን በይበልጥ በመጠቀም ስራቸውን ማዘመን ይጠበቅባቸዋል፡፡
ዓሊ ከሀገሩ ወጥቶ ከ20 ዓመታት በላይ በአሜሪካ ሌላ ስራ ሲሰራ የቆየ ቢሆንም በሀገሪቱ የሙዚቃ እድገት የራሱን አሻራ ያኖረ፤ ታሪክ የሰራ ትልቅ ሰው መሆኑ መቼም አይዘነጋም የሚለው አርቲስት ዳዊት “እኔ ለዓሊ ኬይፋ የምመኝለት ነገር ቢኖር ከዘመኑ ጋር የሚራመድ እራሱን የቻለ ትልቅ የሙዚቃ አሳታሚ ኩባንያ ባለቤት ሆኖ በሀገር ውስጥና በዓለማቀፍ ደረጃ ታዋቂ እንዲሆና ታሪኩን እንዲያድስ ነው፡፡” በማለት ስለ ዓሊ ኬይፋ ያለውን አስተያየት ሰጥቷል፡፡