1 minute read
ፍስሀ ወልደአማኑኤል
የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሄራዊ የእግር ኳስ ቡድን ተጫዋችና በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያን ማህበረሰብ የእግር ኳስ ውድድር መስራች የሆነው ፍስሀ ወ/ አማኑኤል የአሊ የልጅነት ጓደኛ ከነበሩት አንዱ ናቸው ፡፡ በወጣትነት ጊዜያቸው ለአራተኛ ፣ አምስተኛ ፣ ስድስተኛና ሰባተኛ የአፍሪካ ዋንጫ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተሰልፎ የተጫወተው ፍስሃ ወልደአማኑኤል ከሃምሳ ዓመት በፊት ነበር ከአሊ ጋር በዳግማዊ ምኒሊክ ትምህርት ቤት የተዋወቁት ፡፡
Photo by Daniel Tiruneh
Advertisement
“ ከዓሊ ጋር በዋናነት የተዋወቅነውና ጓደኝነታችንም የተጠናከረውሁለታችንም ለቅዱስ ጊዮርጊስ የእግር ኳስ ቡድን በምንጫወትበት ጊዜ ነው ፡፡|” ይላሉ አቶ ፍስሀ፡ ፡ በወቅቱ ዓሊ ከሰው ተግባቢ፣ ሰው የሚወድና ቸር ነበር የሚሉት አቶ ፍስሀ ድሮ አዲስ አበባ ፒያሳ ይገኝ በነበረው ኪንግ ጆርጅ ባር በአብዛኛው የሚዝናኑበት ስፍራ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡
የአቶ አሊን ደግነትና ሰው አክባሪነት በተመለከተ አቶ ፍስሀ በህይወታቸው የማይረሱት ነገር እንዳለ ሲያስታውሱ “ እ.ኤ.አ በኦገስት 1969 ዓ፣ም ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ ስሄድ በሂልተን ሆቴል በርካታ ጓደኞቼን እንድጠራ አድርጎ ከፍተኛ የሽኝት ግብዣ ሸኝቶኛል፡፡ ” ብለዋል፡፡ የአቶ ዓሊ ደግነትና መልካምነት በቃላት አልገልጸውም የሚሉት አቶ ፍስሀ ዓሊ በርካታ ሰዎችን ሲረዳና ሲደግፍ ይመለከቱ እንደነበር፣ እንደ ሙዚቃ አዘጋጅና ነጋዴ ለራሱ ብቻ የሚያስብ፣ ስግብግብ ሳይሆን ለሌሎች መኖርን የመረጠ ድንቅ ሰው ነው ሲሉ ይናገራሉ፡፡
ዓሊ ኬይፋ ወይም በሰፊው ደግሞ ዓሊ ታንጎ በሚል ታዋቂ ስም የሚጠራው ዓሊ ረጋ ያለ፣ ቤተሰቡን የሚወድ፣ ሀገሩን የሚወድና ስራውን የሚያከብር መሆኑ በሁሉም ዘንድ የታወቀ ነው፡፡ እንደዚህ ለሀገርና ለህዝብ ለሰሩ ሰዎች እውቅና እና ክብር መስጠት አስፈላጊ እንደሆነ ሁሉም ያምናል፡፡ አቶ ዓሊ በሀገራችን ለሚገኙ የሙዚቃ ሰዎች ወይም ድምጻዊያን እድገት የራሱን ድርሻ የተወጣ ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጅ በመሆኑ ከፍተኛ ክብርና እውቅና ሊቸረው ይገባል፡፡
“አቶ ዓሊ ክብርና እውቅና ይገባዋል፤ የሚረሳ አይደለም፤ በርካታ ታዋቂ ሙዚቀኞች ለምሳሌ ጥላሁን ገሰሰ፣ መሀሙድ አህመድ፣ ሙሉቀን መለሰ፣ አስቴር አወቀ፣ አሊ ቢራና ሌሎች ሙዚቀኞች ጎልተው እንዲወጡ ያደረገ ባለውለታ ነው፡፡ ትልቅ አስተዋዕጾ አድርጓል፡፡ ሲሉ አቶ ፍስሀ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡